የንባብ ትምህርት ሲሰጥ ለንዑሳን የንባብ ክሂሎች የሚሰጣቸው ትኩረት ፍተሻ
Abstract
አጽርሆተ ጥናት
‹‹የንባብ ትምህርት ሲሰጥ ለንዑሳን የንባብ ክሂሎች የሚሰጣቸው ትኩረት ፍተሻ›› በሚል ርዕስ የተሰራው ጥናት ዋና ዓላማ በንባብ ትምህርት ጊዜ ለንዑሳን የንባብ ክሂሎች የሚሰጣቸውን ትኩረት መፈተሽ ነው፡፡ መሰረታዊ ጥያቄዎቹም ለየትኞቹ የንዑሳን የንባብ ክሂሎች የበለጠ ትኩረት ይሰጣል? የጥናቱ ተተኳሪዎች መምህራንስ ስለ ንዑሳን የንባብ ክሂሎች ያላቸው ግንዛቤ ምን ይመስላል? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ይሞክራል፡፡ በመሆኑም እነዚህን የጥናቱ መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ በጥቅም ላይ የዋሉት የመረጃ መሰብሰቢያ መሣሪያዎች በቪዲዮ ቀረጻ የታገዘ ምልከታ፣ የመምህራንና የተማሪዎች የጽሁፍ መጠይቅ፣ እንዲሁም ቃለመጠይቅ ናቸው፡፡ንዑሳን የንባብ ክሂሎች በተጠኚ መምህራኑ የተሰጣቸው ትኩረት አነስተኛ ነበር፡፡ተጠኚ መምህራኑ ንዑሳን የንባብ ክሂሎችን የሚያስተምሩት በመማሪያ መጽሐፉ ውስጥ ባሉት ንዑሳን የንባብ ክሂሎች ላይ ብቻ የተወሰነ ሆኖ ታይቷል፡፡ በንባብ ትምህርት የአቀራረብ ደረጃዎች ቅድመ ንባብ ደረጃ በተሻለ ሁኔታ የተተገበረ ሲሆን፣በጊዜ ንባብ ደረጃ ያሉ ንዑሳን የንባብ ክሂሎች በአብዛኛው ተዘንግተው ታይተዋል፡፡ ለምሳሌ የዝምታ ንባብ፣የአሰሳ ንባብ፣ የገረፍታ ንባብ ባለመተግበራቸው የንባብ ትምህርቱ ይሰጥ የነበረው በተማሪዎች ወይም በመምህራን እየተነበበ ነበር፡፡ በድህረ ንባብ ደረጃ መዳበር ካለባቸው ንዑሳን የንባብ ክሂሎች የምንባቡን አጠቃላይ ሃሳብ መረዳት ንዑስ ክሂል የንባብ ትምህርት ከሌሎች ጋር ማጣመር ንዑስ ክሂል ከፍተኛ ትኩረት የተሰጣቸው ሲሆን የቀረበውን ምንባብ መገምገም ደግሞ አነስተኛ ትኩረት እንደተሰጠው ጥናቱ አመላክቷል፡፡ መምህራኑም ለንዑሳን የንባብ ክሂሎች ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በመጨረሻም የታዩትን ድክመቶች ለማሻሻል ሊያግዙ ይችላሉ የተባሉ የመፍትሔ ሐሳቦች በመጠቆም ጥናቱ ተቋጭቷል፡፡
ቁልፍ ቃላት፤ የንባብ ትምህርት፣ ንኡሳን ኪሂሎች፣መቀበያ ከሂል፣የንባብ ደረጃ፣ ምንባብ