የሐይማኖት መከባበር እሴቶች፣ በደቡብ ወሎ ዞን ቦረና ወረዳ ማሳያነት
Abstract
የሐይማኖት መከባበር እሴቶች፣ በደቡብ ወሎ ዞን ቦረና ወረዳ ማሳያነት
አህጽሮተጽሁፍየጥናቱ ዋና ዓላማ በደቡብ ወሎ ዞን ቦረና ወረዳ የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በአብሮነት ለመኖር ያስቻሏቸው የመከባበር መገለጫ እሴቶችን ማስተዋወቅ ነው። ጥናቱን ለማካሄድ ያነሳሳኝ ዋናው ምክንያት በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል በታሪክ የተገነባው የብዝሃ-ባህል የግንኙነት መስተጋብር ባሕርያት በዝርዝር ተጠንተው አልተገለፁም፤ ከነዚህ ተጠንተው ካልተገለጹ ባህላዊ እሴቶች መካከል አንዱ በቦረና ማህበረሰብ ያለው ሀይማኖታዊ የመከባበር እሴቶች ይገኙበታል፡፡ ጥናቱ አይነታዊ የምርምር ዘዴን በመጠቀም በገለጻ ስልት ተካሂዷል፡፡ መረጃዎችን ለመሰብሰብ አገልግሎት ላይ የዋሉት መረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች ምልከታና ቃለመጠይቅ ናቸው፡፡ መረጃዎቹ የተሰበሰቡት እሴቶቹ በሚገኙበት ባህላዊና ማህበራዊ ዓውድ ውስጥ ነው፡፡ አጥኚው ለስምንት ወራት ያህል መረጃዎችን ከአካባቢው ተመልክቷል፡፡ በታላሚ ንሞና ዘዴ የተመረጡ ስምንት ሰዎችም በቃለ መጠይቅ በመረጃ አቀባይነት ተሳትፈዋል፡፡ በጥናቱ አገልግሎት ላይ የዋለው የጠቀሜታዊነት ፎክሎራዊ ንድፈ ሀሳብ ነው፡፡ በደቡብ ወሎ ዞን ቦረና ወረዳ ለአብሮነት አስተዋጽዎ ያላቸው የመቻቻል እሴቶች በርካታ ሲሆኑ ዋና ዋናዎቹ በሁለት ፎክሎር ዘውጎች (ሀገረሰባዊ ልማድ፣ማህበረ ፖለቲካዊ ተቋም) ስር ሊጠቃለሉ የሚችሉ ናቸው፡፡ ይሄውም ሀገረሰባዊ መድሀኒት፣ ሀገረሰባዊ እምነትና ሀገረሰባዊ ጋብቻ በሀገረሰባዊ ልማድ ስር ይካተታሉ፡፡ እድር፣ ሀገረሰባዊ ዳኝነትና ጅጌ/አዝማች ደግሞ በማህበረ ፖለቲካዊ ተቋም ስር ይመደባሉ፡፡ በጥናቱ ውጤት መሰረት የሃይማኖት መከባበር እሴቶች ለቦረና ማህበረሰብ የአብሮነት፣ የእርስ በርስ ትስስር ማለት ነው፡፡ በቦረና ማህበረሰብ የጤና እክል የገጠመው ወይም አጋንንት የለከፈው ክርስቲያኑም ሆነ ሙስሊሙ በልቡ አምኖ ጤንነቱን ለማግኘት ወደነዚህ የፀበል ቦታዎች ይሄዳል፡፡ ከጸበላቸው አልፎ እምነታቸውን ይቀበላል፤ በመስቀሎቻቸው ይታሻል፡፡ከጋብቻ አንጻርምየክርስትናወይም የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ መሆን የጋብቻ መስፈርት አይሆንም፡፡ የሙስሊም ልጅ የክርስቲያን ልጅ፡ የክርስቲያንልጅ የሙስሊም ልጅ ታገባለች፤ያገባል፡፡ ሽማግሌዎች
በአዋቂነታቸው፣በታማኝነታቸው፣በትዕግስታቸውና በማህበራዊ ደረጃቸው መሰረት ይመረጣሉ፡፡ ሽማግሌዎቹን ለመምረጥ እስላም ወይም ክርስቲያን መሆን በመስፈርትነት አይወሰድም፤ ክርስቲያኑም ሙስሊሙም ለብቻው ቅሬ ወይም እድር የለውም፤ሁለቱም ይሳተፋሉ፡፡ ክርስቲያኑ፤ ሙስሊሙ ልጁን ሲድር፣ ሙስሊሙም ክርስቲያኑ ሲድር አዝማች ይዞ ከባለጉዳዩ ጋር ለሙስሊም ወይም ለክርስቲያን እንግዶች ድግስ ያዘጋጃል፡፡ ይህም በማህበረሰቡ ዘንድ ያለምንም የሀይማኖት ልዩነት ማህበረሰቡ ተከባብሮና ተቻችሎ በአብሮነት እንዲኖር አስችሎት ቆይቷል፡
ቁልፍ ቃላት፤ሀገረሰባዊ-ልማድ፣ ማህበረፖለቲካዊ ተቋማት፣ ጅጌ/አዝማች፣ እቅሬ